Comments Off on አዲሶቹ የመከላከያና የደኅንነት አለቆች | ሪፖርተር Ethiopian Reporter Amharic

አዲሶቹ የመከላከያና የደኅንነት አለቆች | ሪፖርተር Ethiopian Reporter Amharic

www.ethiopianreporter.com/article/11090

አዲሶቹ የመከላከያና የደኅንነት አለቆች

ከግራ ወደ ቀኝ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አደም መሐመድና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ከግራ ወደ ቀኝ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል አደም መሐመድና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ብዙ ጊዜ በማያጋጥም ክስተት፣ ሁለት ከፍተኛ የአገሪቱን የመከላከያና የደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎችን በአንድ ቀን ተክተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገር መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም የነበሩትን ጄኔራል ሳሞራ የኑስን በክብር ሸኝተው፣ ጄኔራል ሰዓረ መኰንንን በምትካቸው ሾመዋል፡፡

ጄኔራል ሳሞራ በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹምነት ለ17 ዓመታት ያህል የሠሩ ሲሆን፣ በ1993 ዓ.ም. በሕወሓት ውስጥ በተፈጠረ መከፋፈል ምክንያት ከሠራዊቱ የተሰናበቱትን ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ገብረ ትንሳዔ ተክተው ነበር የተሾሙት፡፡ ጄኔራል ሰዓረ ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ከመሆናቸው በፊት የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ሁለቱም ጄኔራሎች የኢሕአዴግ ነባር ታጋዮች ነበሩ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩትን አቶ ጌታቸው አሰፋን፣ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥና ምክትል ጠቅላይ ኤታ ማዦር ጄኔራል አደም መሐመድ ተክተዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ለረዥም ዓመታት በደኅንነት ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡
ጄኔራል ሰዓረና ጄኔራል አደም ከሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የመከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታ ማዦርነትና የብሔራዊ ደኅንነትና መረጃ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነቶችን ተረክበዋል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተከናወነው በጄኔራል ሳሞራ የኑስ የሽኝት መርሐ ግብር ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጄኔራል ሳሞራ የኑስ ከተነገረላቸው ውጪ ብዙ ያልተነገረላቸው ገድሎች የፈጸሙ፣ አገርን ከወራሪ በመከላከል ረገድ ከፍተኛ የአመራርነት ብቃት ያሳዩ ናቸው በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሥጋና አቅርበውላቸዋል፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ወታደርነት ጀግንነት፣ ወታደርነት አገር መጠበቅ፣ ወታደርነት ባንዲራ ማስከበር መሆኑ ቢታወቅም በተለያዩ የፖለቲካ ጉድለቶች የተነሳ ልናፈርሳቸው የሚገቡ በርካታ ግንቦች፣ ልንገነባቸው የሚገቡ በርካታ ድልድዮች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ መፍረስ የሚገባቸው ግንቦች፣ የጥላቻ ግንቦች፣ የዘር ግንቦች፣ የመናናቅ ግንቦች እየፈረሱ የአንድነት ድልድዮች፣ የፍቅር ድልድዮችና የይቅርታ ድልድዮች ሊገነቡ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህንንም የምናሳይበት በአገር መከላከያ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ በተለያዩ ምክንያቶች ከመከላከያ የወጡና ማዕረጋቸውን ያጡ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አዛዥ የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ዓለምሸት ደግፌ በይፋ ማዕረጋቸው ተመልሶ በክብር የሚሰናበቱበት ዕለትም ጭምር ነው፡፡ እንዲሁም ብርጋጄር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእስር ቤት የቆዩ አሁን ከእስር ከወጡ በኋላ ከእነ ሙሉ ክብራቸው ጡረታ የሚወጡበት ዕለትም ጭምር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሁለቱ ካሁን ቀደም ማዕረጋቸው ተገፍፎባቸው የነበሩት ከፍተኛ የጦር መኰንኖች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ በማሴር ክስ ተመሥርቶባቸውና ተፈርዶባቸው በእስር ላይ የቆዩ ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ሌሎች በመከላከያ ያገለገላችሁ፣ በጡረታ የተገለላቸሁ፣ አሁንም አክቲቭ ሆናችሁ እያገለገላችሁ ያላችሁ፣ መከላከያ ብሔር የለውም፡፡ መከላከያ ዘር የለውም፡፡ ለአንድ አገር ለአንድ ባንዲራ ለጋራ የምንሞት መሆናችንን አውቀን፣ በልዩ የፍቅር ስሜት የሚወጡትን እያከበርን የምንሸኝ፣ ያለን የትናንትናውን የምናስታውስ የአንድ አገር ወታደሮች መሆናችንን እንድናስብ እንደዚህ ዓይነት መልካም ፕሮግራም ክቡር ፕሬዚዳንቱ በማዘጋጀት ሁላችንንም ስለሰበሰቡና ሽልማቱን ስላዘጋጁ በእኔና በኢፌዴሪ መንግሥት ስም ላመሠግን እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ከፍተኛ የክብር ሜዳሊያና የኒሻን ሽልማት ለተሰናባቹ ጄኔራል ሳሞራ ያበረከቱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ ‹‹ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሕገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት በአዲስ መልክ በማደራጀት ሒደት ውስጥ ለነበረዎት የጎላ ድርሻ፣ የተጣለብዎትን ሕዝባዊ አደራ በቁርጠኝነትና በኃላፊነት መንፈስ ለመወጣት ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፤›› ሲሉ አሞግሰዋቸዋል፡፡

የኒሻንና ከፍተኛ ክብር መቀበያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጄኔራል ሳሞራ፣ ‹‹ሽልማቱ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ለሕዝቡ ብቻ የሚያገለግል መሆኑ በተግባር ላሳዩ ለመላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አመራርና አባላት የመንግሥትና የሕዝብ ዕውቅና ነው፡፡ ስለሆነም ለዕውቅናው እጅግ የላቀ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ የመከላከያ ኃይላችን ከሕዝብ ተነጥሎ የማይኖር፣ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የወጣ፣ የሕዝቦችን ክብርና ባህል የሚያውቅ፣ የሕዝቦችን ጥቅም የሚያስቀድም፣ አገራችን ኢትዮጵያ የተረጋጋ ሰላም እንዲኖራት፣ የሕዝቦችን ሉዓላዊነት ከማንኛውም ጥቃት የሚከላከል፣ መሥዋዕት እየሆነ ያለና ለዚህ ተልዕኮ መሰዋት ክብር ነው ብሎ የሚያምን፣ የዚህ ሠራዊት አባል በመሆን ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማገልገል ክብር ነው፡፡ ለተሰጠኝ ሽልማትና ክብር ደግሜ የላቀ ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰጧቸው ሹመቶች በተጨማሪ፣ በቅርቡ ከፓርላማ አፈ ጉባዔነት ተነስተው የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው አድርገው ሾመዋቸው የነበሩትን አቶ አባዱላ ገመዳንና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ግርማ ብሩን (አምባሳደር) በጡረታ አሰናብተዋል፡፡

******

Filed in: AMHARIC, News Tags: 

Share This Post

© 2019 Ye Dallas Radio! – የዳላስ ራዲዮ!. All rights reserved.
Site designed by YeDallas Radio!.