Comments Off on ምላሹ የዘገየው የኢትዮጵያዊያን የካሳ እና ይቅርታ ጥያቄ ፣ወደ ቫቲካን ሰዎች – BBC News አማርኛ

ምላሹ የዘገየው የኢትዮጵያዊያን የካሳ እና ይቅርታ ጥያቄ ፣ወደ ቫቲካን ሰዎች – BBC News አማርኛ

 

ምላሹ የዘገየው የኢትዮጵያዊያን የካሳ እና ይቅርታ ጥያቄ ፣ወደ ቫቲካን ሰዎች

የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሃውልት KALKIDAN YIBELTAL
የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሃውልት

ከያኔው ገነተ-ልዑል ቤተመንግስት፣ከዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዝቅ ብሎ ኢትዮጵያ መቼም የማትዘነጋውን የእልቂት ቀን የሚዘክር ባለ 28 ሜትር ሃውልት አለ፡፡

በያመቱ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ስፍራ የካቲት 12 ቀን ይሰበሰባሉ፡፡አባት እና እናት አርበኞች “እመ-ሰቆቃ” ግራዚያኒን በቀረርቶ ያወግዛሉ፣አምስት አመት ጣልያን ታግለው ለሀገሪቱ ዳግም ነጻነትን ያመጡትን ጀግኖች እያነሳሱ በፉከራ ያሞግሳሉ፡፡አንዳንዶቹ ደግሞ የዚህ ሁሉ በደል ፈጻሚ ሀገር መቼ ይሆን ይፋዊ ይቅርታ የምትጠይቀው? እጃቸው ያለበት አካላትስ የካሳ ከረጢታቸው መቼ ይሆን የሚፈታው ? ሲሉ ከንፈራቸውን ይነክሳሉ ::

የካሳ እና ይቅርታ ዘመቻ ወደ ቫቲካን ሰዎች

የሙዚቃ መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀ የማርሽ ባንድ ሰራዊት፣ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች የመጡ ብላቴናዎች ክያኔ፣ለዝክር የመጣው ሰው ስነ-ስርዓቱ ካለቀ በኋላ ቤቱ ገብቶ የሚያወራው አዲስ ነገር አሳጥተውት አያውቁም፡፡

የ2002 ዓመተ ምህረቱ የሰማዕታት ቀን ማግስት አዲስ ነገርን በተመለከተ በአያሌው ዕድለኛ ሳይሆን አልቀረም፡፡

አዲስ አበባ ጀግኖችን አሞግሳ ፤ለሰማዕታት የነፍስ ይማር ጸሎት አድርሳ በተመለሰች ማግስት፣ የካቲት 29-2002 ዓ.ም ፣ መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› የተሰኘ ተቋም በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችን ትብብር የሚጠይቅ የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ይፋ አደረገ።

የዘመቻውን ይዘት ከሚያብራራው ጥራዝ ላይ ትንሽ እንቆንጥር፣

“በ1935-41(እኤአ) ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወርራ ባደረሰችው አሰቃቂ የጦር ወንጀል፣ የቫቲካን መንግስት እጅ ከጓንት ሆና ተባባሪ ስለነበረች፤የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ተጽዕኖ እንዲደረግባት ፣ለዓለማቀፋዊው ህብረተሰብ ፣በዓለም ላሉ መንግስታት ሁሉ ፣ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፤ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣….ለሌሎች ለሚመለከታቸው ድርጅቶችና ለእውነት ለቆሙ ህዝቦች ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ አቤቱታችንን በታላቅ ትህትና እናቀርባለን፡፡”

የዘመቻው ተጽዕኖ ውጤታማ ይሆን ዘንድ፣ 100ሺ ሰዎች ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ተቋሙ በወቅቱ ጠይቋል።

ስምንት ዓመታት አለፉ፣ዘመቻውን የተቀላቀሉ ሰዎች ቁጥር 7ሺ አልሞላም፣ቫቲካንም ይቅርታ አልጠየቀችም።

ከፋሽስት ጣልያን የመርዝ ጭስ ራሱን ለማዳን ጭንብል ያጠለቀ ኢትዮጵያዊ Getty Images
ከፋሽስት ጣልያን የመርዝ ጭስ ራሱን ለማዳን ጭንብል ያጠለቀ ኢትዮጵያዊ

የቫቲካን ዝምታ …የአረጋዊው ቁጭት

ዘመቻው ይፋ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በየአደባባዩ ብቅ እያሉ የዘመቻውን አስፈላጊነት ለማስረዳት ሲለፉ የሚታዩ አረጋዊ አሉ። እኝህ ሰው “ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ” የተሰኘው ተቋም ሀላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ ናቸው ፡፡

የታለመው የፈራሚ ብዛት ካለመስመሩ ጎን ለጎን፣ ቫቲካን ካለወትዋች እስከአሁን ኢትጵያዊያንን ይቅርታ አለመጠየቋ አይወጥላቸውም ፣”ናዚዎች በአይሁዶች ላይ እልቂት ሲፈጽሙ ቫቲካን ዝም በማለቷ ብቻ በክርስቲያናዊ ትህትና አይሁዶችን ይቅርታ ጠይቃለች ፣” ሲሉ የሚያነሱት አቶ ኪዳኔ ፣« እንደ ክርስቲያን ድርጅት ለፈፀሙት የወንጀል ተባባሪነት ይቅርታ መጠየቅ አይበዛባቸውም። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገር ስለሆነች ይሆን ወደኃላ የሚሉት?ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው፣›› ሲሉ ጥያቄ ይመዛሉ፡፡

የተቋማቸውን ስልክ የመታ ሰው ከሚነሳቸው ጥያቄዎች አንዱ ቫቲካን በኢትዮጵያዊያን እልቂት ውስጥ ያላት ተሳትፎ ምን ያህል ነው? የሚል ነው፡፡ ከሌላኛው ጫፍ ብዙ ጊዜ የማይጠፉት አቶ ኪዳኔ የቫቲካንን ተሳትፎ ፤ የይቅርታውን አስፈላጊነት ለማስረዳት አይታክቱም።

“ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ብዙ ወንጀሎች ተፈፅመዋል። አንድ ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ተጨፍጭፈዋል፣ከዚያ ውስጥ በአዲስ አበባ በሶስት ቀናት ብቻ 30ሺ ሰዎች ተጨፍጭፈዋል፣ ከ2ሺ በላይ ቤተ-ክርስቲያኖችና 525ሺ ቤቶች ወድመዋል። ፋሽስት ጣልያኖች ብዙ ዝርፊያ፣ስደት እና እንግልት በኢትዮጵያዊያን ላይ አድርሰዋል።እንዲያ በሚሆንበት ጊዜ ቫቲካኖች ፋሽስት ጣልያኖችን ደግፈዋል፣ባርከዋል ቀድሰዋል፣” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ከታሪክ አዋቂዎች፣ ከንጉሳዊያን ቤተሰቦች፣ ከሃይማኖት አባቶች እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በመሆን ያቋቋሙት ተቋም፣ ቫቲካን ይቅርታ ትጠይቅ ዘንድ የሚለፋው -ይቅርታው ለኢትዮጵያዊያን ስነልቦናዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ካሳን ብሎም ዓለማቀፋዊ ዕውቅና እንደሚያመጣ በማመን እንደሆነ ያብራራሉ።

በተቀናጀ ዘመቻ አቤቱታቸውን ያሰሙ ህዝቦች ለተገቢ ካሳ መብቃታቸውንም ለአብነት ይዘረዝራሉ፣”ጣልያኖች 30ሺ ሊቢያዊያንን በመጨፍጨፋቸው ፣ለዚህ አድራጎታቸው 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ካሳ (በልማት ስራ መልኩ) ለመክፈል ተስማምተዋል፣” በማለት ካለመናገር ደጅ አዝማችነታችን እንዴት እንደተነፈገ ያሰምራሉ፡፡

ይሄ ዘመቻ እንደ ኢትዮጵያ መንግስት እና የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ያሉትን ተቋማት ድጋፍ ቢያገኝ ኖሮ ውጤቱ ይፈጥን እንደነበረ የሚያነሳሱት አቶ ኪዳኔ ፣ዘመቻው ከታለመው የፈራሚዎች ቁጥር እስከ አሁን ድረስ አንድ አስረኛውን አለማግኘቱ የፈጠረባቸውን ቅሬታ አይሸሸጉም፡፡

የጣልያን ጦር ኢትዮጵያን ሲወር Three Lions
የጣልያን ጦር ኢትዮጵያን ሲወር

ዲፕሎማሲን የሚመክረው የአርበኞች ማህበር

“በደም እና አጥንት ግብር ” ሀገራቸውን ያቆዩ እናትና አባት አርበኞች ያቋቋሙት “የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር” በስምንት ዓመታት ውስጥ የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዷል፡፡

ጥቂት የማይባሉት አባላቱን በሞት ተለይተዋል፣ የአስተዳደር ሽግሽግም ተፈጽሟል፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ማህበሩን ይመሩ የነበሩት ሊቀ-ትጉሃን አስታጥቄ አባተ -በልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ተተክተዋል፡፡እንደነበር ከቀጠሉት አንዱ ወኔ ይመስላል፣በማህበሩ መሪ ድምጸት ውስጥ እንደሚሰማው ያለ፣

“የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር የኢትዮጵያ ንብረት የሆነ ሚስማር ጭምር ያለአግባብ ሄዶ እንደሆነ ‘ወደ ሀገሩ መመለስ አለበት’ የሚል ፅኑ የሆነ፣ የማያወላውል አቋም አለው ፣” ይላሉ ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን የቫቲካን እና የይቅርታው ጉዳይ ሲነሳ፣ የጋለ ድምጸታቸው መልሶ ይሰክንና በተጀመረው አይነት መንገድ ካሳ እና ይቅርታን የመጠየቅ ሂደት ውስጥ ማህበራቸው ሊሳተፍ እንደማይችል ይናገራሉ። ለዚህ የሚሰጡት ምክንያት ማህበሩ የተመሰረተበት ህግና ደንብ ከላይ የተጠቀሰውን ዓይነት ዘመቻ ለመከወን የማያስችል መሆኑ ነው።

ከሁሉም ከሁሉም ግን የማህበሩ ፕሬዚደንት በግለሰቦች አስተባባሪነት እዚህ የደረሰው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ውጤታማ ስለመሆኑ ጥርጣሬ አላቸው።በጋርዮሽ ተፅዕኖ የመፍጠር ሙከራ ይልቅ በመንግስታት መካከል የሚደረግ ንግግር ፍቱን መፍትሄ እንደሚያመጣ ለማሳየት ባቀደ መልኩ፣ “የአክሱምን ሀውልት የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ሄዶ አላመጣውም … ዲፕሎማሲ እንጂ” ይላሉ፡፡

ቫቲካን ‘አላት’የሚባለውን የግፍ ተሳትፎንም ልጅ ዳንኤል ጆቴ ይጠራጠሩታል፣ “እኛ እንደምንረዳው( የጣልያንን ጦር) ባርኮ የላከው ሚላኖ ላይ የነበረ ቄስ ነው። የአቶ ዘውዴ ረታን መፅሃፍ ላይ ራሱን የቻለ ታሪካዊ መግለጫ አለው(አቶ ዘውዴ ረታ አምባሳደር በነበሩበት ወቅት ተመራምረው እና ጥናት አድርገው የፃፉት መፅሃፍ ነው)። አንዳንድ ታሪኮችን በስሜታዊነት ተነስቶ ከማየት ርቀን፣ አንስተን እና አውርደን በደንብ ተዘጋጅተን የቀረብን ጊዜ ጣልያኖችም ሆነ እንግሊዞች ነገሮችን የማይመልሱበት ፣የተጠየቁትን የማያደርጉበት ምንም ምክንያት የለም፣”ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር በዘመቻው ላይ ያለውን የፍሬ ነገር ጥርጣሬ ያጋራሉ፡፡

የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ሃላፊ ልጅ ዳንኤል ጆቴ

የኢትዮጵያ አምላክ፣ይረዳናል!

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ‹ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ› ሃላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ ድምጽ ውስጥ ሀዘን ተጠልሏል፡፡በልጅ ዳንኤል ጆቴ በኩል የተሰጠው ምላሽ እንዳልተዋጠላቸው ያሳብቃል፡፡

“ለፍትህ ጉዳይ ሁላችንም ሃላፊነት አለብን።እንኳን እኛ ኢትዮጵያዊያኑ ይቅርና ጣልያኖች ሳይቀሩ እየደገፉት ያለ ጉዳይ ነው።በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ ማለት ለአገር የሚያኮራ ጉዳይ አይደለም፣” ሲሉ ይመክታሉ፡፡ የቫቲካን ተሳትፎ ላይ ጥያቄ መነሳቱም ቢሆን ለእሳቸው እንቆቅልሽ ነው፣ “ብዙሃኑ ጳጳሳት ወርቃቸውን ሳይቀር እያወጡ ለጦርነቱ አስተዋፅኦ ያደረጉ መሆኑን፣ አንደኛው ‹ካርዲናል› ይሄ ጦርነት ቅዱስ ጦርነት ነው ሲሉ የተናገሩት መረጃ አለን፣ የጣልያን ጦር አዲስ አበባ ሲገባ የደስታ መግለጫ ካወጡት መካከል የመጀመሪያው (የቫቲካኑ) ፖፕ ሃያስ ነበሩ፡፡ ይሄንና ሌላ ማስረጃዎችን ያየ ..እንዲህ ያለ የማይሆን ነገር ለመናገር አይችልም፣” ሲሉ ይሟገታሉ፡፡

አቶ ኪዳኔና አጋሮቻቸው ከእኒህ ሁሉ ዓመታት በኃላ “ይሄ ነገር አይሰምርም” ብለው መዝገባቸውን ለማጠፍ ዝግጁ አይደሉም፡፡ ከዚህ ቀደም በቫቲካን ተባባሪነት ለደረሰ በደል፣ የነዋይ ካሳን እና ይፋዊ ይቅርታን ማግኘት እንዲሁም በወቅቱ የተዘረፉ ቁሳቁሶች እና ቅርሶች ወደሀገራቸው ተመላሽ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረታቸው እንደሚቀጥል ይናገራሉ።

ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ -የተሰኘው ተቋም ሀላፊ ኪዳኔ ዓለማየሁ

በእነ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ መንደር የተስፋ ጀምበር አልጠለቀችም ፡፡በዚህ ዓመት ህዳር ወር ላይ ከ81 ዓመት በፊት የካቲት 12 ለተፈጠረው እልቂት ሰበብ የሆነው ሩዶልፎ ግራዚያኒ መታሰቢያ ሃውልት ‘አፊል’ ከተሰኘችው የሮማ ጎረቤት ከተማ እንዲነሳ ተወስኗል፡፡

ሃውልቱ እንዲሰራ የገንዘብ ፈሰሱን ያጸደቁት የከተማዋ ከንቲባ እና ሁለት የአስተዳደር አባላት ‹‹ፋሽስት ይቅርተኝነት›› Apologia del Fascismo የሚሰኘው ህግ ተጠቅሶ በስምንት እና ስድስት ወራት እስር እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡

ሃውልቱ መወገድ እንዳለበት ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ሲጎተጉቱ ከነበሩ ተቋማት አንዱ ለሆነው ‘ዓለማቀፍ ህብረት ለፍትህ -ለኢትዮጵያዊያን ጉዳይ’፣ውሳኔው የሌሎች ዘመቻዎች ተስፋም ፈጽሞ እንዳልከሰመ የሚያሳይ ምልክት ይመስላል፡፡

ሃላፊው የ ቫቲካን ይቅርታ መዘግየት የሚያብከነክናቸውን ያክል አንድ ቀን ይቅርታው እንደሚሰማ ያላቸውን ዕምነትም ከፍተኛ ነው፡፡ ይሄን የሚደግፈው የሚደጋግሙት ሀረግ ነው ”የፍትህ አምላክ፣የኢትዮጵያ አምላክ፣ይረዳናል!” የሚለው፡፡

 

******
Filed in: AMHARIC, News Tags: 

Share This Post

© 2019 Ye Dallas Radio! – የዳላስ ራዲዮ!. All rights reserved.
Site Designed by YeDallas Radio!.