Comments Off on Statement on Dallas Meeting re Fascist War Crimes in Ethiopia and Required Justice

Statement on Dallas Meeting re Fascist War Crimes in Ethiopia and Required Justice

Statement on Dallas Meeting re Fascist War Crimes in Ethiopia and Required Justice-1

10/20/2013          For PDF Version Click Here

ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸሙት ግፍና ስለሚጠበቀው ፍትሕ በዳላስ ከተማ የተከናወነ ውይይት

የውይይቱ አስተናባሪ፤ አቶ ይልማ ዘርይሁን፤ በዳላስ የኢትዮጵያውያን መረዳጃ ማሕበር ሬዲዮ ያቀረቡት መግለጫ

ፋሺሽቶች በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸሙት የጦር ወንጀል፤ ሁለት ኢጣልያውያን ፊልም እያዘገጁ ነው።

“በመጀመሪያ ለሰጣችሁኝ እድል ከልብ አመሰግናለሁ።

የዳላስ/ፎርት ወርዝ የኢትዮጵያውያን  የጋራ መረዳጃ ማሕበር እና ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕየኢትዮጵያ ጉዳይ  GLOBAL ALLIANCE FOR JUSTICE:  THE ETHIOPIAN CAUSE (www.globalallianceforethiopia.org) ፋሽስት ኢጣልያኖች በኢትዮጵያ ላይ ስለ ፈጸሙት ግፍና ስለሚያስፈልገው ፍትሕ እንዲሁም ስለ ጉዳዩ በዶክመንታሪ መልክ ስለሚዘጋጀው ፊልም፤ ኤል.ቢ.ጄና ኮይት ላይ በሚገኘው ግራንድ ሆቴል፤ ቅዳሜ፤ October 19, 2013፣ ከሰዓት በኋላ 3:00 pm እስከ 6 ፒ. ኤም ተከናውኗል።

ግሎባል አላያንስ የድጋፍ አባላቱ የሚገኙት፣  በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ቦታዎች ሲሆን፣ በዳላስና ፎርትወርዝ አካባቢ ደግሞ የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ አለው። በትናንትናው እለት የተዘጋጀው ፕሮግራም በዚሁ ድጋፍ ሰጪ ኮሚቴ ሲሆን ዋናው አቀነባባሪና የዚህ ጉዳይ ተጠሪ የዳላሱ አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ናቸው።

ከአርባ አምስት በላይ ታዳሚዎች የተገኙበት ይህ የትናንትናው ኮንፈረንስ በሰዓቱ ተጀምሮ በሰዓቱ ሲያልቅ በአካሔዱና በውጤቱ ሁሉም የተደሰቱ መሆናቸውን ከስብሰባው ፍጻሜ በኋላ የተገኘው ፊድባክ ወይም አስተያየት ያመለክታል።

በስብሰባው ላይ የተገኙት ግለሰቦች በእድሜ፣ በጾታና፣ በታሪክ አዋቂነት ከሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የሚወከሉ መሆኑ ደግሞ ከተሰጡት አስተያየቶች በተጨማሪ መገንዘብ ተችሏል።

የወቅቱ ተናጋሪዎች ከአስራ አምስት ያላነሱ ሲሆኑ ፤ ተዘጋጅተው ከቀረቡት መካከል ዋና ዋናዎቹን እንደሚከተለው አቀርባለሁ።  ከላይ እንደጠቀስኩት የኢትዮጵያውያን የጋራ መረዳጃ ማሕበርና የዓለም አቀፍ ሕብረት ፍት በጋራ የተዘጋጀ በመሆኑ የመረዳጃ ማሕበሩ ኤግዘክዩቲቭ ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ብርሀን መኮንንና፣  የግሎባል አላያንስ ተጠሪ አቶ ኪዳኔ ዓለማየሁ ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል።

በትናንተው ስብሰባ ከአሥራ አምስት ያላነሱ አዛዉንት፣ በመካከለኛ እድሜ ላይ ያሉ የዳላስ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም የሀይማኖት መሪዎችና ወጣቶች፣ ተራ በተራ ተነስተው፣ በዘመዶቻቸው፣ በወላጆቻቸውና በአያቶቻቸው ላይ የደረሰውን በደል በቁጭትና በምሬት እንዲሁም በሀይለቃል፣ በግጥምና፣ በንባብ አቅርበው ቤቱን አስለቅሰዋል።

ከማሕበሩና ከሕብረቱ ሌላ የፊልሙ ዝግጅት መሪ ሚስተር ቫለሪዮ ቺሪያቺ እንዲሁም የካሜራ ቀራጭ ባልደረባው ሚስተር አይዛክ ፊልም ከማንሳት ተግባራቸው በተጨማሪ ለታዳሚዎቹ የጥያቄና መልስ እድል ሰጥተዋል። በዚህ አጋጣሚ፤ እነዚህ ሁለት ኢጣልያውያን ፊልም ቀራጮች፤ እስካሁን ድረስ፤ ኢጣልያ የሚገኙትን የኢትዮጵያውያን ማሕበር መሪዎችንና የፋሺሽቶች ተቃዋሚ የሆኑ ኢጣልያውያንን እንዲሁም ኢትዮጵያ በመጓዝ አዲስ አበባ ያሉትን የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር መሪዎችን በተጨማሪም ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመሔድ የሰማእታቱን አጽምና አንድ የዓይን ምስክር የሆኑ አባት አነጋግረው ፊልም ማንሳታቸው ታውቋል።

ምናልባት አንዳንዶቻችሁ እንደሰማችሁት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የፋሽስት ኢጣልያን የግፍ ወረራ ሲፈጽም በሕዝባችን ላይ ያደረሰው አሰቃቂ በደል በቅጡ በታሪካዊ መልክ ያልተዘገበ መሆኑ ተሰምቷቸው እነዚህ ሁለት ወጣት የጣልያን ተወላጆች በራሳቸው ወጪ ዶክመንታሪ ወይም ታሪካዊ ፊልም ለመቅረጽና የተከናወነውን ኢሰብአዊ ወንጀል በፊልም ለመተረክ ተነስተዋል።  የትናንትናውም አመጣጥ ለዚሁ ፊልም ትረካ የሚረዳ አንዳንድ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ነበርና ዓላማቸው በሚገባ የተሳካላቸው መሆኑን ገልጸውልናል።

ለፍትሕና ለመሠረታዊ የሰው ልጅ መብት የሚደረገው ትግልና አቤቱታ እነሆ ለብዙ ዓመታት ማለትም ከጣልያንን ወረራ በኋላ ለሰባ አምስት ዓመታት ያህል አስቆጥሯል።

በየዓመቱ የካቲት 12ትን አስመልክቶ ይህ ጉዳይ ሲዘከር ቢከርምም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግሎባልአላያንስፎርኢትዮጵያ አማካኝነት ትግሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሰራጭ ተደርጓል። ባለፈው የካቲት 2012 በሰላሳ ከተሞች ውስጥ የተከናወነው ሰላማዊ ሰልፍና ኮንፈረንስ እንዲሁም የተላለፉት መግለጫዎችና የአቤቱታ ደብዳቤዎች የዚህ ትግል ምሳሌዎች ናቸው።

እየተቀረጸ ያለው ዶክመንታሪ ፊልም እንደአዘጋጅዎቹ ከሆነ በኢጣልያም ሆነ በሌሎች አገሮች የሚገኙ ወጣቶችና አዳዲስ ትውልዶች የግራዚያኒን ጭፍጨፋ ለማወቅ እድል ስላላገኙ ታሪኩ እንዲጋለጥና ተዳፍኖ እንዳይቀር ፍላጎታቸውን ከገለጹ በኋላ፣ አገራቸው ኢጣልያ በፋሽቱ ወረራ ጊዜ ባደረሰችው በደል እንደሚያፍሩበትና ይቅርታ መጠየቅና ካሳም መከፈል እንዳለበት ማመናቸውን አስረድተዋል።

በትናንትናው ስብሰባ ላይ ከቀረቡት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ግሎባል አላያንስ ይዞ የተነሳው አምስት ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው።

  1. ኢጣልያ ካሳ መክፈል እንዳለባት
  2. የተዘረፈብን ንብረት ሰነዶችንም ጨምሮ እንዲመለሱልን (ሬስቲቱሽን)
  3. ቫቲካን ሌሎቹን የተበደሉ አገሮች ይቅርታ እንደጠየቀችው ሁሉ ኢትዮጵያንም ይቅርታ እንድትጠይቅ
  4. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይህንን የፋሽሽት በደል እንደበደል አድርጎ በኦፊሻል ደረጃ መዝግቦ እንዲይዘው
  5. ለግራዚያኔ እየተገነባ ያለው ሀውልት እንዲፈርስ ወይም ደግሞ ማፍረስ ካልፈለጉ መታሰቢያነቱ ለሌላ እንዲሆንና በሌላ ስም እንዲሰየም

በተጨማሪም ከኢትዮጵያውያን በትንሹ የሚጠበቀውም የሚከተለው እንደሆነ አቶ ኪዳኔ አስረድተዋል።

  1. በዚህ ማሕበር ውስጥ መግባትና ድጋፍን መስጠት
  2. የተዘጋጁ አቤቱታዎችን (ፒቲሽኖች) በግሎባላላያንስፎርኢትዮጵያ.ኮም በመሄድ መፈረም
  3. በሚቀጥለው የካቲት 12 የመታሰቢያ ክብረበዓል ላይ ከሃምሳ ያላነሱ ከተሞች እንዲሳተፉ ስለሚደረግ የስብሰባ ወይም የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ሲደረግ እዚያ ላይ መሳተፍ ናቸው።

ልዩ ምስጋና በመጀመሪያ ጥሪውን አክብረው ለመጡት ታዳሚዎች በሙሉ ፣ ከዚያም ለአቶ ብርሀን መኮንን የኢትዮጵያውያን የጋራ መረዳጃ ማሕበርን በመወከል የጽሁፍ ዝግጅት በማቅረቡ፣  ለወ/ሮ ራሄል ታደሰ ልብ የሚነካ ግጥም በማቅረቧ፣ ለአቶ ይርጋለም ጎበዜ፣ ልዩ ልዩ የታሪክ ፊልሞችንና ዶክመንታሪዎችን በማቅረብ እንዲሁም ልብ የሚመስጥ ንግግር በማድረግ፣ ለዲያቆን ክንፈ – ከእስራኤል አገር ለጉብኝት የመጡ የሃይማኖት መሪ፣ ለሚስተር ቫለሪዮ ቺሪያቺና ለአይዛክ፣ ለአቶ ሄኖክ አሰፋ ለእንግዶች እንክብካቤ በማድረግ። በመጨረሻም ለአቶ ኪዳኔ አለማየሁ።

http://globalallianceforethiopia.org/

ዘውገና ስጦታው አመሰግናለሁ።”

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Filed in: Audio Archive, Links, Must Read, News, Radio Tags: 

Share This Post

© 2019 Ye Dallas Radio! – የዳላስ ራዲዮ!. All rights reserved.
Site designed by YeDallas Radio!.